ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ፓርቲ በደቡብ ወሎ በደረሰ ጥቃትና በጋሞ ዞን የጎርፍ አደጋ ላይ የሐዘን መግለጫ አወጣ

Posted on 2026-03-11 10:34:34


“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ፓርቲ በደቡብ ወሎ በደረሰ ጥቃትና በጋሞ ዞን የጎርፍ አደጋ ላይ የሐዘን መግለጫ አወጣ

አዲስ አበባ፡- “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ፓርቲ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መሐል ሳይንት ወረዳ በምትገኘው ጥንታዊቷ ታዕካ ነገሥት አትሮንስ ማርያም ገዳም ላይ ተፈጽሟል ባለው ጥቃት እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰ የጎርፍ አደጋ ላይ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት የገዳሙ አበምኔትን ጨምሮ 6 የገዳሙ አገልጋይ አባቶችና እናቶች ሥርዓተ ቅዳሴ ሲወጡ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ 28 የሚደርሱ አባቶችና ምዕመናን ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

መግለጫው በተጨማሪ በደቡብ ወሎ የምትገኘው ጥንታዊቷ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት እየተፈጸመ እንዳለ መረጃ መድረሱን ጠቅሶ፣ እንዲህ ዓይነት ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ፓርቲው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በየካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በተጣለ ከባድ ዝናብ የተነሳ በተፈጠረ የናዳና የጎርፍ አደጋ የ30 ያህል ሰዎች ሕይወት ማጣታቸውን ገልጿል።

ፓርቲው በመግለጫው ለሞቱት እረፍተ ነፍስ፣ ለተጎዱት ፈጣን ማገገም እና ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናት በመመኘት፣ ዜጎችም ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።


አስተያየትዎን ይተው