Posted on 2026-03-11 07:35:36
አዲስ አበባ፡- ከ11 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ቀጣሪ ድርጅቶችን በቀጥታ ለማግኘት በተዘጋጀ የሥራ ፈጠራ ዓውደ ርዕይ እንደሚሳተፉ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው እንደገለጸው፣ ዓውደ ርዕዩ የከተማዋን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና ሥራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ታስቦ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሦስት ቀናት ይካሄዳል።
በዓውደ ርዕዩ ላይ ከ200 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ተሳታፊ ድርጅቶቹም በተለያዩ ዘርፎች ያሉ የሥራ ዕድሎችን ለወጣቶች በማቅረብ በቀጥታ የቅጥር እድል እንዲያገኙ ይረዳሉ ተብሏል።
በዓውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ ቢሮው የሥራ ፈጠራ እድሎችን በማስፋፋት የከተማዋን የሥራ አጥነት ችግር ለመቀነስ በተለያዩ አሰራሮች እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ሥራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የሚያግዝ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዘርጋቱ ለሁለቱም አካላት ምቹ የግንኙነት መደላድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በዓውደ ርዕዩ ወቅት ከተሳታፊ ወጣቶች መካከል 4 ሺህ የሚሆኑ በቀጥታ የሥራ ትስስር እንዲያገኙ ይጠበቃል ሲል ቢሮው አመልክቷል።