ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮች ይጀምራሉ

on | 2026-03-09 10:21:59

Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin


ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮች ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፡– ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በ16 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉባቸው የክርክር መድረኮች እንደሚጀምሩ አስታወቀ። መድረኮቹ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለሕዝብ ተደራሽ እንደሚደረጉም ቦርዱ ገልጿል።

ይህ መረጃ የተገለጸው ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር በተካሄደ “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያላቸው ድርሻ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው። በዚህ ውይይት ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አካታች እና ታማኝ ምርጫ ለማካሄድ ቦርዱ እያከናወነ ያለው ስራ ምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቧል።

በውይይቱ ላይ ቦርዱን ወክለው የተሳተፉት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ እንደገለጹት፣ የመራጮች ምዝገባ በአንዳንድ ክልሎች መጀመሩን እና የእጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ በዘንድሮው የምርጫ ሂደት ውስጥ የሚያከናውነው ትልቁ ስራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚካሄዱባቸውን የክርክር መድረኮች ማዘጋጀት መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት፣ በአሁኑ ጊዜ በቴሌቪዥን በኩል የሚተላለፉ የፖለቲካ ክርክሮች ቢኖሩም እነዚህ በሚዲያ ተቋማት የራሳቸው ተነሳሽነት የሚዘጋጁ መድረኮች ናቸው፤ ስለሆነም የተለያዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አላቸው።

በዚህ ምክንያት ቦርዱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉባቸውን በጥራት የተዘጋጁ የክርክር መድረኮች እያዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። መድረኮቹ ፓርቲዎች እንደ እጩዎቻቸው ብዛት በመደበኛ ሁኔታ የሚሳተፉባቸው መሆናቸውም ተገልጿል።

ቦርዱ እንደገለጸው፣ በ16 የተለያዩ ዋና ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ እነዚህ የክርክር መድረኮች በተለያዩ ቋንቋዎች እና የስርጭት ዘዴዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ይደረጋሉ። ይህም መራጮች ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ መረጃ እንዲያገኙ እና በተገቢ ግንዛቤ ላይ ተመስርተው ውሳኔ እንዲወስኑ እንደሚያግዝ ተጠቁመዋል።


አስተያየትዎን ይተው