ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

ስምረት ፓርቲ በትግራይ እየተካሄደ ነው ያለውን ኢ-ህጋዊ የሀራጅ ሽያጭ እንዲቆም ጠየቀ

on | 2026-03-05 00:37:46

Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin


ስምረት ፓርቲ በትግራይ እየተካሄደ ነው ያለውን ኢ-ህጋዊ የሀራጅ ሽያጭ እንዲቆም ጠየቀ

አዲስ አበባ -  የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በትግራይ እየተካሄደ ነው ብሎ የገለጸውን ኢ-ህጋዊ የሀራጅ ሽያጭ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ።

ፓርቲው የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በጽሑፍ ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ የህዝብ ሀብት የሆኑ ንብረቶች በግልጽነት የጎደለ መንገድ በውስጥ ሀራጅ ለመሸጥ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ፓርቲው እንደገለጸው፣ ለጦርነት ወጪ ማሟላት ተብሎ የተፈጥሮ ሀብቶች እየተመዘገቡ እና የገጠርና የከተማ መሬቶች ያለ አግባብ እየተሸጡ ነው ብሏል።

በአንድ በኩል የየካቲት ወር ደሞዝ እንዳይከፈል ትእዛዝ መውጣቱን ሲጠቅስ፣ በሌላ በኩል ከመንግሥት ሰራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ 20 በመቶ እንዲቆረጥ መመሪያ መሰጠቱን ጠቁሟል።

በሀራጅ ሊሸጡ ከተባሉ ንብረቶች መካከል የመቐለ ኤፍኤም ጽሕፈት ቤት፣ መነን ሆቴል፣ ሜጋ ሕትመት፣ ፖሊስ ኦኬስትራ እና በኲሐ የሚገኘው ትርንጎ ሆቴል እንዳሉ ገልጿል። እነዚህ ንብረቶች የህዝብ ሀብት ስለሆኑ በህግ ወደ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ እንደማይፈቀድ አስጠንቅቋል።

ፓርቲው ባለሀብቶችና ባንኮች በዚህ ሂደት እንዳይሳተፉ ጥሪ ሲያቀርብ፣ በኢ-ህጋዊ ጨረታ የሚሳተፉ አካላት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቅቋል። በተጨማሪም የትግራይ ህዝብ በተደራጀ መንገድ ይህን አሰራር እንዲከታተልና እንዲቃወም ጥሪ አቀርቧል።


አስተያየትዎን ይተው