ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

ኢሰመኮ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸውን በይፋ አስታወቀ

on | 2026-03-05 00:04:33 on2026-03-05 01:29:10

Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin


ኢሰመኮ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸውን በይፋ አስታወቀ

አዲስ አበባ - ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በተፈጸሙ የጥቃት ድርጊቶች ምክንያት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸውን በይፋ አስታወቀ።

ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ የካቲት 19 በሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ እና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ሌሎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ተደርሶባቸዋል። በተጨማሪም እገታ፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት መከሰቱ ተገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሰጡት መግለጫ፣ በአርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሰዎችን መኖር መብት እንዲሁም በሰላም እና በደኅንነት የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለማካሄድ ያላቸውን መብት እያጡ መሆናቸውን ገልጸው ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ እገታ፣ ማፈናቀል እና ዘረፋ የተለመዱ ክስተቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ኮሚሽነሩ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ ጥቃት በተፈጸመባቸው እና አሁንም የጥቃት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች በቂ የጸጥታ ኃይሎችን እንዲያሰማሩ ጠይቀዋል።  

በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች አስቸኳይና በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ ጥሪ አቀርበዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው በደህንነት ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እና ተመሳሳይ ጥቃቶችን ቀድሞ ለመተንበይና ለመከላከል የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።

ኢሰመኮ በአካባቢው የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ እና ተጠያቂዎች ህግ ፊት እንዲቀርቡ በመንግሥታት ላይ ግዴታ መኖሩን አስጠንቅቆ፣ የዜጎች ደኅንነትና መብት ጥበቃ ቀዳሚ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቋል።


አስተያየትዎን ይተው