on | 2025-12-24 11:34:15
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዜጎች የመደራጀትና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት ሕገ-መንግሥታዊ መብት በአንዳንድ ክልሎች መጣሱን በመግለጫ አስታወቀ።
ቦርዱ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 31 እና በምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ዜጎች የመደራጀትና የፓርቲ የመመሥረት መብት እንዳላቸው ቢደነግግም፣ ይህ መብት በተግባር መከልከሉ ተገልጿል።
መግለጫው እንደሚያመለክተው፣ “የኮንቶማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” መሥራቾች በጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በቡታጅራ ከተማ የመሥራች ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ሁሉንም ሕጋዊ ሰነዶች አሟልተው ለቦርዱ ቢያሳውቁም፣ የከተማው የፀጥታ አካላት “ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ስር ናት” በሚል ምክንያት ጉባዔውን እንዳይካሄድ አግደዋል። በዚህ ሂደት የፓርቲው መሥራች አባላት ከአዳራሽ ተወግደው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቦርዱ ከታዛቢዎቹ ሪፖርት መረዳቱን ገልጿል።
በተመሳሳይ መልኩ “የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” መሥራቾችም ታኅሣሥ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በሀድያ ዞን ቢጠና ታዳጊ ከተማ የመሥራች ጉባዔ ለማካሄድ ሲዘጋጁ፣ የከተማዋ የፀጥታ አካላት ስብሰባው እንዳይካሄድ እና የፀጥታ ድጋፍ እንደማይደረግ በመግለጽ ጉባዔውን አቋርጠዋል።
ቦርዱ እንደገለጸው፣ በአዋጅ ቁጥር 1133 አንቀጽ 27(1) መሠረት ማንኛውም የፌደራል ወይም የክልል የመንግሥት አካል ከቦርዱ ለሚቀርብለት ሕጋዊ ጥያቄ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለበት። ነገር ግን በሁለቱም ጉዳዮች ይህ ግዴታ እንዳልተፈጸመ ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ ይህን ድርጊት የፖለቲካ ምኅዳርን የሚያጠብ እና ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ተግባር መሆኑን በመጠቆም፣ በየደረጃው የሚገኙ የክልል የመንግሥት አካላት በዜጎች የመደራጀትና የፓርቲ የመመሥረት መብት ላይ የሚፈጸሙ መሰናክሎችን እንዲያቆሙ እና ተገቢ የዕርምት እርምጃ እንዲወስዱ በጥብቅ አሳስቧል።
በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው "ጊፋታ”
በቶኪዮ የወርቅ መርገም አልሰበር ያላት ኢትዮጲያ