on | 2026-02-27 07:51:59 on2026-03-01 14:08:35
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ – ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በወቅታዊ የአገር ሁኔታ ላይ ያወጣው መግለጫ፣ በተለይ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ንጹሓን ላይ የሚደርስ ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
መግለጫው በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ በድሮንና በከባድ መሣሪያ የተፈጸመ ጥቃት በርካታ ንጹሓን እንዲሞቱና ከፍተኛ ንብረት እንዲወድም መደረጉን ጠቅሷል። በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦርና ወረታ ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ ንጹሓን መገደላቸውን እና የጤና ተቋማት በእሳት መውደማቸውን አመልክቷል።
ትብብሩ በንጹሓን ላይ የሚደርስ ማንኛውንም ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ “መንግሥት በሕግ ማስከበር ሽፋን የሕዝብን መከራ እያከበደ ነውን?” ሲል ጥያቄ አቅርቧል። በተፋላሚ ወገኖች በኩል የአገልግሎት ተቋማት ውድመትና እገታ መፈጸም እንዲሁም ከማኅበረሰብ እሴት ያፈነገጠ እንደሆነ ገልጿል። ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ (ዛይሴ) በየካቲት 8 እና 9 2018 ዓ.ም በተፈጠረ ግጭት ከ21 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን ጠቅሷል። የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት ችግሩን በሕጋዊና ዘላቂ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ ቀርቧል።
በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አደገኛ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ትብብሩ፣ አዲስ የጦርነት ግንባር እንዳይከፈት እና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን በወንበራ ወረዳ አካባቢ ከየካቲት 1 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ነዋሪዎች “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራ ቡድን ቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና ሕዝቡ መፈናቀሉን፣ ንብረት መዘረፉን እና ዜጎች መገደላቸውን ጠቅሷል።
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን መርቲ ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ወራጃርሶ ወረዳ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰዎች መገደላቸውና ቤቶች መቃጠላቸው ተገልጿል። መንግሥት ዜጎችን መጠበቅ ካልቻለ በሕጋዊ መንገድ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
በመጨረሻ፣ የሚዲያ ተቋማት ተደጋጋሚ መዘጋትና የጋዜጠኞች ፈቃድ መነጠቅ ከሕገ መንግሥት መርሆዎች ጋር የሚጣረስ መሆኑን ገልጿል። መንግሥት የሕዝብን መረጃ የማግኘት መብት እንዲያከብር አሳስቧል።