on | 2025-11-18 13:45:18 on2025-12-01 00:20:13
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ:- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኛ ምዘና እና ምደባ ሊያካሂድ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሰራተኛ ቅነሳ ሊያደርግ እንደሆነ የተሰራጨው መረጃም ትርጉም የማይሰጥ መሆኑንም አመላክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የ75ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩ አከባበር እና የራስገዝነት ሪፎርም አፈፃፀምን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህም ወደ ራስገዝነት የሚያደርገው ሽግግር የእስካሁን ጉዞ፤ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ እና ቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ሳሙኤል (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የሠራተኞች ምደባና ሥምሪት ማስፈፀሚያ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ፣ ውይይት ተደርጎበት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በዚህም የሰራተኛ መልሶ ሥምሪትና ምደባ የሚከናወንበት የጊዜ ሰሌዳ ፀድቆ ለሚመለከታቸው አካላት ተልኳል ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ፤ ለሰራተኞች መመዝገቢያና የመረጃ ማጥሪያ ኦንላይን ፎርም ተዘጋጅቶ ምዝገባ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
እንደ ሳሙኤል (ዶ/ር) ገለጻ፤ ከደረጃ 08 በላይ ላሉት አንድ ሺህ 500 ለሚደርሱ የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች ፈተና በመስጠት ብቃትና ውጤታማነትን ማዕከል በማድረግ ምደባ ይሰጣል፡፡
ሌሎች ከደረጃ 08 በታች ላሉ የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች በሰነድና በነበራቸው የግምገማ ውጤት በውድድር ምደባ እንደሚሰጥ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም የአካዳሚክ ሰራተኞች፣ ተመራማሪዎች፣ የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳቶች እና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጤና ሙያተኞች በውድድር ላይ የተመሰረተ ልየታ በማድረግ ስምሪት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ የሰው ኃይል በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ የተዘጋጀውን የመውጫ ስትራቴጂ በመመርኮዝ ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እንደሚከናወንም ጨምረው ገልጸዋል።
ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ጋዜጠኞች ዩኒቨርሲቲው ሰራተኞቹን ሊቀንስ ነው ተብሎ የተሰራጨውን መረጃ በሚመለከት ላቀረቡላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፤ የተሰራጨው መረጃም “ትርጉም የማይሰጥ” ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም በዩኒቨርሲቲው 4 ሺህ የአስተዳደር ሰራተኞች ያሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነሱም በተዘጋጀው የሰራተኛ ስምሪት ማዕቀፍ መሰረት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው በሁሉም መዋቅሮች “በቂ ሰራተኛ አለ ማለት ሁሉም ይቀጥላሉ ማለት አይደለም፤ በቅድሚያ ብቃት ያላቸው ሰራተኞች ቦታውን መያዝ አለባቸው” ብለዋል፡፡
ዘገባው የጋዜጣ ፕላስ ነው
በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው "ጊፋታ”
በቶኪዮ የወርቅ መርገም አልሰበር ያላት ኢትዮጲያ