አዲስ አበባ - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪክ ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ
ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት 19 ሺሕ 800 ጋብቻዎችና 5 ሺሕ 805 ፍቺዎች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጥጋቡ ሹምዬ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በሰጡት መግለጫ፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች የፍቺ ማስረጃ እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠየቁ ከዚህ ቀደም ዘግይተው ያልተመዘገቡ ፍቺዎች እንዲመዘገቡ አስችሏል ብለዋል።
ከተመዘገቡት ፍቺዎች መካከል 1 ሺሕ 750 የሚሆኑት በፍቺው ከተፈጸመ በ30 ቀናት ውስጥ የተመዘገቡ ሲሆን፤ 695 ደግሞ ዘግይተው የተመዘገቡ መሆናቸው ተገልጿል።
ይህ ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ2 ሺሕ በላይ ጭማሪ እንዳሳየ ኤጀንሲው አመልክቷል።
በፍቺ ምክንያቶች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የህግና ማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ መቅደስ አስፋው እንደሚሉት፤ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች ድንገተኛ አይደሉም፤ ነገር ግን ተገቢ ትኩረት ካልተሰጣቸው የሚያድጉ እና በመጨረሻ ወደ ፍቺ የሚያመሩ ናቸው።
እርሷ ተጨማሪ በማለት፤ ጋብቻን መመስረትም ሆነ መፍረስ የግለሰቦች ምርጫ ቢሆንም፣ ከፍቺ በኋላ የሚከተሉ አውዳሚ ውጤቶች ቀላል እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል። ፍቺ በቀጥታ ተጋቢዎችንና ልጆችን የሚጎዳ ሲሆን፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ የማኅበረሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ ያዳክማል ብለዋል።
እንዲሁም ልጆች በወላጆቻቸው ግጭትና መከራ ውስጥ ሲያድጉ የማንነት ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አስጠንቀቀዋል። ይህም በማኅበረሰብ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ወደ ግለኝነት እንዲመራ እና የአገር እድገትን እንዲያዘገይ ይችላል ብለዋል።
የፍቺ መጠንን ለመቀነስና ሕፃናትን ከሥነ-ልቦና ችግር ለመጠበቅ ዋና መፍትሔ የቅድመ ጋብቻ ዝግጅት መሆኑን አመልክተዋል። ተጋቢዎች ከጋብቻ በፊት ለኃላፊነት ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና የግልና የአካባቢ ተጽዕኖዎችን አስቀድሞ መለየት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።