አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋና ጸሐፊ ምስጥረ-ስልኣሴ ታምራት በቅርቡ በሚካሄዱ የምርጫ ክርክሮች ላይ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ገለልተኝነታቸውን እንዳጡ በመግለጽ በተለይም አንዳንዶቹ የገዢውን ብልፅግና  ፓርቲ አጀንዳ እያጎሉ እንደሚታዩ አስታወቁ።

በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ወ/ሮ ሚስጥረሥላሴ ታምራት በተለይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በሚያቀርቧቸው የምርጫ ክርክሮች አቀራረብ ላይ ግልጽ የሆነ ወገንተኝነት እንዳስተዋሉ ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የክርክር መድረኮቹ በተለይ በአዲስ አበባ እየተፈጸሙ ባሉ የ“ኮሪደር ልማት” ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እነዚህን ፕሮጀክቶች በማስተዋወቅ መልኩ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል። እርሳቸው ግን እነዚህ ፕሮጀክቶች በከተማው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ እንደሚታሰብ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተዘጋጀውን እና በ“ቱሪዝም፣ ማዕድንና ኢንዱስትሪ” ላይ ያተኮረውን የክርክር መድረክ ላይ እንደተሳተፉ የገለጹት ዋና ጸሐፊዋ፣ የመድረኩ አቀራረብ ራሱ የአርታኢ ነፃነት ላይ ጥያቄ እንዳስነሳ አስታውቀዋል።

“በክርክሩ ወቅት ተቋሙ ክርክሩን በሚመራው ባለሙያ በኩል እነዚህን ፕሮጀክቶች መቶ በመቶ ሲያስተዋውቅ እንደነበር ተመልክቻለሁ። እኔ እንደ ጋዜጠኛ የቦታ መረጣና የእይታ አቀራረብ በኮምኒኬሽን ውስጥ ትልቅ የሆነ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ በደንብ አውቃለሁ::

ዋና ጸሐፊዋ በተጨማሪም በቀረጻው ወቅት የተናገሩት ሚዲያዎቹ ገለልተኛ እንዳልሆኑ የሚጠቁሙ ንግግሮች ከመጨረሻው ስርጭት እንደተቆረጡ አስታውቀዋል።

“በቀረጻው ወቅት ይህ አቀራረብ ተገቢ እንዳልሆነ እና ቢያንስ በምርጫ ወቅት ሚዲያዎች እንዲህ ያለ ግልጽ ወገንተኝነት ማሳየት እንደማይገባ ተናግሬ ነበር፤ ነገር ግን ያ ክፍል ከስርጭቱ ተቆርጧል።” ብለዋል።

በተጨማሪም እርሳቸው ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በምርጫና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ቃለመጠይቅ ፈጽሞ እንዳልተላለፈ አስታውቀዋል።

“አዲስ ቲቪ በምርጫ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢሕአፓን ወክዬ የሰጠሁትን ቃለመጠይቅ ሙሉ በሙሉ አፍኖ አስቀርቶታል። ይህ ድርጊት ስለ ሚዲያ ተቋሙ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ።”

ወ/ሮ ሚስጥረሥላሴ ታምራት የህዝብ ሚዲያ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ መሆን እንደማይገባ በመግለጽ፣ በተለይም በምርጫ ወቅት ገለልተኝነት ሊጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ፓርቲያቸው በምርጫ ሂደቱ ውስጥ መቀጠሉን ከሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነትና የሚዲያ ነፃነት አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ግን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬት በክርክር መድረኮች አስተባባሪነት ያሳየውን ፕሮፌሽናሊዝም አድንቀው አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት አካል ሆነው የሚካሄዱ የፖለቲካ ክርክሮች በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በቴሌቪዥን እየተላለፉ ሲሆን ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን ለሕዝብ ለማቅረብ የሚጠቀሙባቸው መድረኮች መሆናቸው ታውቋል።