አዲስ አበባ፦ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው የጦርነት ውጥረት እየተባባሰ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለሥራ ጉብኝት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መጓዛቸው በዲፕሎማሲ ዘርፍ ትኩረትን ስቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በይፋ እንዳስታወቀው፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ትናንት ሐሙስ ለሥራ ጉብኝት ወደ ኤሜሬቶች ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቡዳቢ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በወታደራዊ ዘብ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ የኤሜሬቶች የዜና ወኪል ባሰራጨው መረጃ መሠረት፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በአቡዳቢ ሲደርሱ በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የፍትህ ሚኒስትር አብዱላህ ሱልጣን ቢን አዋድ አል ኑኢሚ እና በሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በቀጠናው ያለው የጦርነት ሁኔታ እየተወሳሰበ ባለበት ወቅት መካሄዱ ተጨማሪ ትኩረት አስገኝቷል። በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ፤ ኢራን በቀጠናው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ያሉባቸውን አገራት በሚሳይልና በድሮን ጥቃት አፀፋ እየመለሰች መሆኑ ተዘግቧል።
በዚህ ሁኔታ በርካታ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸው ታውቋል፤ ነገር ግን አንዳንድ አየር መንገዶች በቀጠናው ያሉ ዜጎቻቸውን ለማውጣት ልዩ የመመለሻ በረራዎችን እያዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ኤሜሬቶች ከመጓዛቸው በፊት በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከአካባቢው መሪዎች ጋር ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል። በዚህም መሠረት ከጅቡቲና ከሶማሊያ ፕሬዚዳንቶች ጋር የተካሄደ ውይይት እና በጅቡቲ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት የተዘጋጀ የኢፍጣር ግብዣ መካፈላቸው የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በተለያዩ የመረጃ ምንጮች ተጋርተዋል።
ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት፤ የጉብኝቱ ዋና አላማ የኢትዮጵያና የኤሜሬቶች የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማጠናከር እንዲሁም በቀጠናው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በቅርብ መወያየት መሆኑን ይጠቁማሉ።