on | 2026-02-24 16:36:57 on2026-03-01 14:08:36
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ–መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከየካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰረዝ መወሰኑን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ እንደገለጸው፣ አዲስ ስታንዳርድ በተደጋጋሚ የሚዲያ ሙያ ስነ–ምግባርን የሚጣስ፣ የኢትዮጵያ ሕጎችን የማይከተል እና የሀገርና የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አደጋ ሊያመጡ የሚችሉ ዘገባዎችን በመስራትና በማሰራጨት ላይ መገኘቱ በሬጉላቶሪ ክትትል መረጋገጡን ገልጿል። በዚህም ላይ ከዜጎች በርካታ ጥቆማዎችና ቅሬታዎች እየቀረቡ መቆየታቸው ተጠቅሷል።
ባለሥልጣኑ በተለያዩ ወቅቶች ተቋሙ እንዲታረም እና ከአጥፊ አካሄዱ እንዲቆጠብ ምክርና ማሳሰቢያ መስጠቱን አስታውሷል። በተጨማሪም የሙያ ስነ–ምግባርን እና የሀገርና የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅምን አክብሮ እንዲሰራ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለመታረም ፈቃደኛ አልሆነም ብሏል።
በመሆኑም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት የተቋሙ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከየካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰረዝ መደረጉ ተገልጿል። ከዚህ ቀን ጀምሮም አዲስ ስታንዳርድ ምንም ዓይነት የሚዲያ ፈቃድ ወይም እውቅና እንደሌለው ባለሥልጣኑ ለሁሉም አካላት አሳውቋል።
ባለሥልጣኑ በመጨረሻ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሁሉ የሕግና የሙያ ስነ–ምግባር መመሪያዎችን በጥንቃቄ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል።