on | 2026-02-24 13:35:53 on2026-03-01 14:08:31
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ የፊስካል ፌድራሊዝምና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር የታለመ አገራዊ የውይይት መድረክ በሂልተን ሆቴል ተካሄደ። መድረኩ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በዓለም ባንክ ትብብር መካሄዱ ታውቋል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የፊስካል ፌድራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ የክልሎችንና የወረዳዎችን የበጀት አቅም ለማጠናከር ዋና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ ውሃ አቅርቦትና በገጠር መንገዶች ዘርፍ የታዩ ልማታዊ ውጤቶች የዚህ ሥርዓት አስፈላጊነትን እንደሚያሳዩ አመልክተዋል።
መንግስት እያካሄደው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ የፊስካል ፌድራሊዝምን መሠረት እንደሚያጠናክር ተገልጿል። ይህም የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ፣ የቅድሚያ ስራዎችን በመለየትና የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርን በማሻሻል ክልሎች የልማት አቅማቸውን እንዲጎልበቱ እድል እንደፈጠረ ተጠቁሟል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው መድረክ የናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የህንድ እና የጀርመን የፊስካል ፌድራሊዝም ተሞክሮዎችን ያካትታል። ከፌዴራልና ከክልል መንግስታት የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመድረኩ በመሳተፍ ያልተማከለ የበጀት አስተዳደር ሥርዓት በቀጣይ እንዴት እንደሚጠናከር ላይ ሀሳብ እንደሚሰጡ ተገልጿል።