on | 2026-02-16 19:59:38 on2026-03-01 17:28:11
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ - ብሔራዊ ባንክ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያው ላይ በ19 ዋና ጉዳዮች ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥ ትልቁ ለውጥ የፎርዋርድ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ያለ ባንኩ ቅድመ ማረጋገጫ እንዲካሄድ መፍቀዱ ነው።
ይህ ማለት ላኪዎች እና አስመጪዎች ከባንኮች ጋር ቀድሞ በመስማማት ወደፊት የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ በዛሬ ዋጋ መዋዋል ይችላሉ ማለት ነው። በዚህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ከፍና ዝቅ መሆን ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ስጋት አስቀድሞ ለመቆጣጠር ይረዳል ተብሏል።
የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ጥላሁን ግርማ እንደሚሉት፣ መመሪያው በተግባር ሲተገበር አስመጪዎችና ላኪዎች በምንዛሪ መለዋወጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን ኪሳራ ለመቀነስ አስፈላጊ ሚና ይጫወታል። ከዚህ በፊት የዶላር ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን ከተፈቀደ በኋላ የብር ዋጋ መዳከም ብዙ ነጋዴዎችን ለኪሳራ እንዳጋለጠ ያስታውሳሉ።
እንዲሁም አዲሱ ማሻሻያ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በውጭ ሀገር መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር አመቺ አልነበረም ብለዋል።
በተጨማሪም በአገልግሎት ዘርፍ ውጭ ምንዛሪ የሚያመጡ ተቋማት ከወጪ ንግድ የሚያገኙትን ገቢ ሙሉ በሙሉ በሪቴንሽን ሂሳባቸው ያለ ጊዜ ገደብ እንዲይዙ መፍቀዱ ለዘርፉ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ይፈጥራል ተብሏል።
ባለሙያዎች አንዳንድ ማሻሻያዎች ለረጅም ጊዜ የሚጠየቁ እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ከመውጣታቸው በላይ በተግባር እንዲተገበሩ ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል።