on | 2026-02-13 10:05:54
Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin
አዲስ አበባ - ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የፍቺ ቁጥር ለመቀነስ ፣ የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ሰርተፊኬት ሳይዝ ማንም ሰው ወደ ጋብቻ እንዳይገባ የሚያደርግ አሰራር ሊጀምር መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ተናገረ።
አሰራሩ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በመመካከር ሥራ ላይ የሚውል ነው ተብሏል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሮበሌ ይህንን አሰራር በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት አድርገናል ብለውናል።
ለተጋቢዎች የቅድመ ጋብቻ ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ በቤተሰብ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሥራቸውን ውጤታማ ለማድረግ የጋራ ፎረም መመስረታቸውንም አቶ ተስፋዬ ነግረውናል።
ፎረሙ በቤተሰብ አስተዳደር በኩል ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን ለመሙላት ይሰራል የተባለ ሲሆን በመንግስት በኩልም መሰራት ላለባቸው ነገሮች ምክረ ሃሳብና ጥቆማ ይሰጣል ተብሏል።
ለብዙ ትዳሮች መፍረስ ዋነኛው ምክንያት ስለ ትዳር ያለው የግንዛቤ ዕጥረት ነው ያሉን አቶ ተስፋዬ ሮበሌ፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት የስልጠና ማኗሎችን መዘጋጀታቸውን ነግረውናል።
ለሀገር ለውጥ ከቤተሰብ መጀመር አለብን ያሉት ኃላፊው በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦች እንዳሉም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት የትዳር ፍቺ ከአለፉት አመታት አንፃር 54 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።