ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ6 ወራት ከ320 ቢሊየን ብር በላይ ብድር አቀረበ

on | 2026-01-27 08:46:21

Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ6 ወራት ከ320 ቢሊየን ብር በላይ ብድር አቀረበ

አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመተግበር ለደንበኞቹ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገለጸ።

ባንኩ የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት መክፈቻ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሲያካሂድ፣ በመርሐ ግብሩ የገንዘብ ሚኒስትርና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሕመድ ሺዴ፣ ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

አቶ አሕመድ ሺዴ በመርሐ ግብሩ ላይ በሰጡት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተግባር ላይ ያዋለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተጨባጭና የሚታዩ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 10.2 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ንግድ ባንክ በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው አስፈላጊ ሚና በመገንዘብ፣ ባንኩን ለማጠናከርና ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በበኩላቸው የባንኩ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፣ ደንበኛ ተኮር የአገልግሎት ሥርዓትን በመተግበር የአገልግሎት ጥራትንና ፍጥነትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ ከ45 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማስተናገድ የቁጠባ ባህልን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት አስፈላጊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ኤፍሬም እንደገለጹት፣ ባንኩ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ከ320 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ማቅረብ ችሏል፤ በተመሳሳይ ወቅትም 36.19 ቢሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቧል።

ባንኩ በሥራ ሂደቶች ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችን በፍጥነትና በግልጽ አሰራር ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 1.69 ትሪሊየን ብር መድረሱንና ጠቅላላ ሀብቱም 2.3 ትሪሊየን ብር መሻገሩን አስታውሰዋል። በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ በመሰብሰብ፣ አጠቃላይ ተቀማጩን 2 ትሪሊየን ብር ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ባንኩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን በማስፋፋት፣ ከሚከናወኑ ጠቅላላ ግብይቶች 90 በመቶ በላይ በዲጂታል መንገዶች እንዲፈጸሙ መድረሱን ተገልጿል።


አስተያየትዎን ይተው