ከይር ቮክስ አፍሪካ

ከይር ቮክስ አፍሪካ

ዜና የሀገር ውስጥ

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባሉ

on | 2025-12-15 20:39:19

Share: Facebook | Twitter | Whatsapp | Linkedin


የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባሉ

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው በ #ኢንቨስትመንት እና በ #ሳይበር_ደህንነት ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተጠቁሟል

ህንድ በመጪው የፈረንጆቹ 2026 የብሪክስ ጉባዔን በሊቀመንበርነት ለመምራት በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት፣ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪካዊ የተባለለትን ጉብኝት ከታህሳስ 7 እስከ 8/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚያደርጉ የኤዥያን ኒውስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።

ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ትኩረት በሚሰጥባቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች ማለትም በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በማዕድን ልማት፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በሳይበር ደህንነት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በጉብኝታቸው ወቅት በተጨማሪም በኢትዮጵያ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

አምባሳደር ራይ፣ ጉዞውን የሁለትዮሽ ትብብርን የሚያጠናክርና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማሻሻያ እንዲሁም የብሪክስ አጀንዳዎችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት የሚያጎለብት “በጣም ታሪካዊ ወቅት” ሲሉ ገልጸውታል።

አያይዘውም “ህንድ እና ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየ፣ ጥልቅና ወዳጃዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለት የስልጣኔ ሀገራት ናቸው” ያሉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የመጀመሪያው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብለዋል።


አስተያየትዎን ይተው